- ፩ - “ተረት ተረት …” “የላም በረት …” “… ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ ነበረ። ሲኖር ሲኖር ቆይቶ ከሌሊታት አንድ ሌሊት ህልም አለመ። አዲስ ልብስ የለበሰ ይመስለዋል። አዲስ ጫማም አድርጎአል። ወላጅ እናቱ በሚያብረቀርቅ ጠርሙስ አዲስ ወተት ሞልተው ይሰጡታል። እሱም ወተቱን ተቀብሎ በለምለም ሳር ላይ እየተራመደ ያንን የወተት ጠርሙስ ይዞ ከአንድ እጅግ ያማረ ውብ ቪላ ውስጥ ሲገባ ህልም አለመ። ህልሙ ከዚያ በላይ አልቀጠለም …” - ፪ - ህልመኛው ሲነቃ በተለመደችው የቁርበት ምንጣፉ ላይ ጋደም ብሎ ነበር። እንደተጋደመ ለጥቂት ደቂቃዎች ስለ ህልሙ አሰበ። “ወተት በጠርሙስ ይዞ የተዋበ ቪላ ውስጥ መግባት” ምን ይሆን ትርጉሙ? ርግጥ ነው ልጁ ለህልም እንግዳ አልነበረም። ይህ ህልም ግን መንፈሱን ኮረኮረው። ሊረሳው ቢሞክርም አልቻለም። … ቪላው በአይነህሊናው ይከሰታል። ወላንሳ በወላንሳ ላይ የተደራረበ፣ በመስታወት ግድግዳ የተገጠገጠ ሰፊ አዳራሽ። ትኩስ ወተት በጠርሙስ … ምን ይሆን? - ፫ - ወጣቱ ህልሙን ችላ ብሎ ማለፍ ቢቸግረው ለጓደኛው አጫወተው። አጫውቶት ሲያበቃም እንዲህ ሲል አሳረገ፣ “… ይህ ህልም ከኔ መጪ ሕይወት ጋር የተቆራኘ መስሎ ተሰምቶኛል። በርግጥ ህልም ብዙውን ጊዜ በተቃራኒው ስለሚፈታ ሳያሳስበኝ አልቀረም። ምንም ይሁን ምን ግን ይህ ህልም አንድ ምስጢር ይዟል …” ጓደኛውም እንዲህ ሲል ማፅናኛ አዘል መፍትሔ አቀረበ፣ “እንዳልከው ያየኸው ህልም ተራ ህልም አይመስልም። ጥልቅ ይዘት እንዳለው አያጠያይቅም። ህልም በታቃራኒው ይተረጎማል ብለህ መስጋትህ ግን ልክ አይመስለኝም። ህልም እንደፈቺው ነው የሚባል ነገርም አለ። የሚሻለው ግን እትዬ ወርቄ ጋር ሄደህ ህልሙን እንዲፈቱልህ ብታማክር ነው። እሳቸው የፈቷት ህልም መሬት ጠብ አትልም …” - ፬ - እትዬ ወርቄ በማለዳ የመጣባቸውን ልጅ እግር እንግዳ በትህትና ተቀብለው፣ ህልሙንም በጥሞና አዳመጡት። አዳምጠው ሲያበቁም የወርቅ ጥርሳቸውን ብልጭ እያደረጉ፣ ህልም አላሚው ላይ ቱፍ ቱፍ አሉበት። እናም እንዲህ ሲሉ ህልሙን ፈቱለት፣ “ልጄ! ምንም ምስጢር የለውም። ወተቱ ወተት ነው። ያማረ ቪላ ያልከውም የአማረ ቪላ ነው።” ፍቺውና ማብራሪያው ይተነተናል ብሎ ወጣቱ በጉጉት ጠበቀ። እትዬ ወርቄ ግን ህልሙን ከዚያ ያለፈ ሊፈቱት ሳይችሉ ቀሩ። ህልመኛው የእትዬ ወርቄን አባባል ፍቺ ብሎ መቀበል ስለተቸገረ በጥያቄ ያጣድፋቸው ያዘ፣ “እትዬ ወርቄ! ወተቱ እንዴት ወተት ብቻ ሊሆን ይችላል? ቪላውስ የማነው?” “እንዳልኩህ ነው የኔ ልጅ። ወተቱ ወተት ነው። ቪላው የማን እንደሆን አላውቅም። ባውቅ ለምን ብዬ እድብቅሃለሁ?” “ከወደፊት ሕይወቴ ጋር ይያያዛል?” “አላውቅም የኔ ልጅ።” - ፭ - ከስድስት ወራት በሁዋላ፣ ህልመኛው የህልሙን ፍቺ ራሱ ደረሰበት። አንዲት ላም ነበረቻቸው። ወለደችና ወተት ተገኘ። በአራተኛው ቀን ማለዳ እናቱ ከእንቅልፍ ቀሰቀሱት። ሲነቃ በወተት የተሞላ ጠርሙስ ጠረጴዛው ላይ ተቀምጦ አየ። ማሰብ ከመቻሉ በፊትም እንዲህ የሚል ትዕዛዝ ደረሰው፣ “ፈጠን በል! ተነስና ይህን ወተት እነ አቶ ሃብታሙ ቤት አድርስ!” ተስፋዬ ገብረአብ
|