አርባ ቀኔ ሆነ ከተለየኋችሁ፣ ድምጼን ከሰማችሁ ዓይኔንም ካያችሁ፣ ከጠየቃችሁኝ ካነጋገርኳችሁ፣ አርባ ቀኔ ሆነ ከሄድኩኝ ትቻችሁ። ምን አደረጋችሁ እኔ ከተለየሁ፣ ጉልበቴ ከከዳኝ ትንፋሼንም ካጣሁ፣ ዝናብ ካረጠበኝ፣ ፀሐይም ከመታኝ፣ ከተለየኋችሁ አርባ ቀኔ ሆነኝ። ለአርባው ፍትሃት በሚዘጋጀው ዝግጅት ላይ ውድ
ባለቤቱ እንድታነብለት ያሰበውን ግጥም
የመጀመሪያውን ክፍል ጽፎ አረፍ አለ። አልጋ ውስጥ
ሆኖ ሰው ያለ አይመስልም። ስጋው ከላዩ አልቆ አጥንቱ
ብቻ ቀርቷል። ፈገግታው ግን ያው ነው። አንዳንዴ
ሃሳብ ይዞት ጭልጥ ይላል። ምን እያሰበ ይሆን? ባለፈው ወር ዶክተሩ ነቀርሳ (ካንሰር) እንዳለበት
ሲነግረው ምንም የመደንገጥ ሁኔታ አላሳየም።
እንዲያውም በደስታ ነው የተቀበለው። ለነቀርሳ
የሚሆነውን መድኃኒት ትጀምራለህ ሲባል ሳያቅማማ
ነበር እሺ ያለው። መድኃኒቱ ጎፈሬ የነበረውን ፀጉሩን
መድምዶ ባዶ ራስ አድርጎታል። ፊቱን በመስታወት ሲመለከተው "ጣዕረ ሞት መስያለሁ አይደለም
እንዴ?" ብሎ ራሱን ጠየቀ። መልስም ሳይጠብቅ
በፈገግታ አለፈው። ተመልሶ ያወጣና ያወርድ ጀመር። እንዴት ሕይወት አጭር ናት? ያሳለፈው የሕይወት
ዘመኑ በሙሉ መጥቶ ድቅን አለበት። ዓይኑን ጨፍኖ
ወደ የወጣትነት ሕይወቱ ነጎደ። የአደገበት ቄዬ ሁሉ
ትዝ አለው። ሀ ... ሁ ያስቆጠሩትን ቄስ አሰባቸው።
አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱን አስታወሰ። ሁለተኛ
ደረጃ፣ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ሁሉም ነገር ትዝ አለው። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ ነበር
ከኢሕአፓ የተዋወቀው። አስራ አንደኛ ክፍል ...።
ጓደኞቹ ሁሉ ወደ የኢሕአፓ፣ የወጣቶች ክንፍ
ኢሕአወሊ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ወጣቶች
ሊግ) ገብተው ነበር። ይህ ጭቁን ሕዝብ፣ ይህ ድሃ
ገበሬ ከጭቆና ነፃ መሆን አለበት ብለው አስረዱት። በመጀመሪያ በወጣት ማኅበር መሳተፍ ጀመረ። እያደር
እየገባበት ሄደ። የኢሕአፓ የወጣቶች ክንፍ
(ኢሕአወሊ) ውስጥ አባል ሆነ። አንድ ላይ ሆነው
ትግላቸውን ቀጠሉ። ቀይ ሽብር ተጀመረ። በመጀመሪያ
ብዙዎቹ ታሰሩ። ጓደኞቹ እስር ቤት ሆነው መልዕክት
ላኩበት። "ከሐረር ጥፋ። በጣም እየፈለጉህ ነው። የት እንዳለህ አልነገርናቸውም። ግን አንተን ለማግኘት
የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ስለእኛ አታስብ።
ነፍስህን አድን! ..." መልዕክቱን እንደሰማ እሱን ላለማጋለጥ ብለው
የተሰቃዩትን እያሰበ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።። እጁን
ሰጥቶ እነርሱን ለማዳን አሰበ። እጁን ቢሰጥም ልዩነት
እንደሌለው ተረዳው። ሐረርን ለቆ ጉዞውን ቀጠለ።
አዲስ ማንነት፣ አዲስ መታወቂያ፣ አዲስ የይለፍ
ወረቀት ተዘጋጀለት። ጉዞ ወደ ሱማሌ ...። ያለመደው በረሃ እግሩን አቃጠለው። ውሃ ጥማቱ ... ረሃቡ ...
ስቃዩ ... ሁሉም ያሳለፈው ችግር በሙሉ አሁን ትዝ
አለው። "ያኔ ነበር መሞት የነበረብኝ" ብሎ
አጉረመረመ። ወረቀቱን አንስቶ ግጥሙን ቀጠለ። ትንሽ ጊዜ ስጠኝ ትንሽም ታገሰኝ፣ ብዬ ብጠይቀው ሞት አልሰማህ አለኝ። ትንሽ ጊዜ ቢያገኝ የሚሠራቸውን ማውጣት ማውረዱን
ቀጠለ። ስለ እናት አባቱ፣ ስለ ልጆቹ ያወጣና ያወርድ
ጀመር። በሕይወት የመኖር ፍላጎቱ ጨመረ። ምትን
ለመደውን እንዲህ ብሎ ቋጠረው። እናቴን ልቅበራት አባቴን ልቅበረው፣ ልጆቼን ላስመርቅ ብዬ ብማጸነው፣ ሞት አልሰማህ አለኝ ምንም ብማለደው። ሶማሌ ውስጥ እያለ ብዙዎቹ ጓደኞቹ በቀይ ሽብር
እንደተገደሉ ከሠፈሩ በቅርብ የተሰደደ አግኝቶ
ነገረው። ስለጓዶቹ ሲያስብ እንባውን በጉንጮቹ ላይ
አለማቋረጥ ይወርድ ጀመር። ሞታቸውን የሰማ ጊዜ
ደጋግሞ ቃል የገባው ታወሰው። የጀመርነው ፍፃሜ
ሳያገኝ ትግሉን አላቆምም ብሎ በእነርሱ ስም ምሎ የተገዘተው ዓይኑ ላይ ድቅን አለበት። ቃል የገባው
ፍፃሜ ሳያገኝ አልጋው ውስጥ ሆኖ ጉልበት አጥቶ ሞቱን
በመጠበቅ ላይ በመሆኑ ምርር ብሎ አለቀሰ። "ወይ ነዶ
..." ብሎ በቀይ ሽብር ስለተሰዉት ጓደኞቹ እያሰበ
አጉረመረመ። "አዎ በቅርብ እንገናኛለን። ዶክተሩ
እንደማልተርፍ ነግሮኛል። እኔም ካሁን ወዲህ በዚህ ምድር ምንም የቀረኝ ነገር የለም። እንዲያውም ቶሎ
ወደ እናንተ መጥቼ ባገኘኋችሁ" ብሎ ፈገግ አለ። በሕይወት ውስጥ የደረሰበትንና ያከናወነውን አሰበ።
ጓደኞቹን በሰማይ ቤት ሲያገኛቸው ምን
እንደሚነግራቸው፣ ምን እንደሚደብቃቸው ማውጣት
ማውረድ ጀመረ። እነርሱ እኮ ይሄን ጊዜ ኢሕአፓ
ሥልጣን ላይ ወጥቶ፣ ሀገራችን ዴሞክራሲ የሰፈነባት
ሀገር ሆናለች ብለው ይጠብቁ ይሆናል፤ እነርሱ እኮ ይሄኔ ኮምኒዝም ዓለምን የለወጣት ይመስላቸው
ይሆናል፤ እነርሱ እኮ ዓለም የላብ አደሮች ሆናለች
ብለው ያስቡ ይሆናል፤ እነርሱ እኮ የሀገራችን ገበሬ
ያለፈለት ይመስላቸው ይሆናል ... እነርሱ እኮ ይሄኔ ...
ብዙ ነገር ያስቡ ይሆናል። ሃሳብ ይዞት ጭልጥ አለ።
ከቀብሩ በኋላ ምን እንደሚፈጠር አሰበ። እንደገና የጀመረውን ግጥም መጻፉን ቀጠለ። ምን አዲስ ዜና አለ? ማንንስ አመመው? ማንንስ ረዳችሁ፣ አለ የቸገረው? ቃል ገብታችሁ ነበር የቀብሬ ለታ፣ ህልሜንስ ሰማችሁ በማንስ ተፈታ? ወይስ ሁሉም ተበተነ ሄደ ወደቤቱ፣ ወይስ ሃሳብ ገባው እሱም ስለሞቱ? አርባ ቀኔ ሆነ እንግዲህ ከሄድኩኝ፣ እቅፍ አድርጌአቸው ልጆቼን ከሳምኩኝ። ስለሀገሬ ጉዳይ አንስቼ ካወጋሁ ፣ ስለልጆቼ መብት ከተከዝኩ ከሰጋሁ፣ ስለአንድነቷም ከጓዴ ካወራሁ፣ አርባ ቀኔ ሆነ ልሳኔንም ካጣሁ። በጎኔ ከተኛሁ አርባ ቀኔ ሆነኝ፣ ጉልበቴ ከከዳኝ አፈር ከተጫነኝ፣ መኖርም ካቆምኩኝ ማለምም ከተውኩኝ፣ ብቻዬን ካደርኩኝ ዓይኔን ከገለጥኩኝ፣ የልጆቼንም ሳቅ ድምፅ ከሰማሁኝ። እንደገና በኢሕአፓ ውስጥ የተደረጉትን ክፍፍሎች
ያወጣና ያወርድ ጀመር። ጓደኞቹ በቀይ ሽብር
የተገደሉት ገና የመጀመሪው ክፍፍል በኢሕአፓ ውስጥ
እንደተፈጠረ ነው። በውልም ለምን ክፍፍሉ
እንደተከሰተ ላያውቁ ይችላሉ። ከዛም በኋላ
ስለተፈጠሩት ክፍፍሎች ማውጣትና ማውረድ ...። ክፍፍል ሁል ጊዜም ድርጅቱን የገደለ ጉዳይ ነው ብሎ
ኀዘን ገባው። መቼ ይሆን ከዚህ የክፍፍል አባዜ
የምንወጣው? ራሱን ጠየቀ። ብዙ ማድረግ የነበረበትን
ሳያደርግ በመቅረቱ ኀዘን ገባው። እንዲህ ብሎ
ቋጠረው። ጨክኜም አይደለ እኔ በልጆቼ፣
በእናቴ በአባቴ በእህት ወንድሞቼ፣
በዕድሜ ልክ ወዳጄ በትግል ጓዶቼ ፣
ከሞት ተደራደርኩ እንግዲህ ላንድ ዓመት፣ እንዲሰጠኝ ጊዜ የትም ላልሄድበት። ከዛም ወደ ሰሜን አሜሪካ እንዴት እንደመጣና በሰሜን
አሜሪካ እንደገና ፓርቲውን በሙሉ ልቡ ለመርዳት
አብሮም ለመታገል እንደተቀላቀለ ታሰበው።
በተቻለው መጠን ደከመኝ ሳይል ይታገል ጀመር።
በፓርቲው ውስጥ አዲስ ክፍፍል ተጀመረ።
አንደኛውን ክፍል ተቀላቀለ። በተለይ የሚወዳቸው ጓዶቹ በሌላው ክፍል መሆናቸው አሳዘነው። ግን ምንም
ማድረግ አልቻለም። ... ንዴት ... ንዴት ... ለበሽታ
ጣለው። አሁን ይኸው ሞቱን እየጠበቀ ነው። ምንም
ድካም ቢሰማውም ያለውን ኃይል አጠራቅሞ መጻፉን
ቀጠለ። አንድ የመጨረሻ ኑዛዜ ለቀሪ ጓዶቹ ለመተው
ሃሳብ መጣለት። ውድ ጓዶች! ይህ የኑዛዜ ቃሌ ነው። ለቤተሰቤ የማወርሰው ምንም
ንብረት ስለሌለኝ ኑዛዜ አያስፈልገኝም። ገንዘቤም
ንብረቴም ብዬ ፍቅሬም ለድርጅቴ ሰጥቼ ከወጣትነት
ዘመኔ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ደፋ ቀና ስል ያፈራሁት
ንብረት የለኝም። ስለዚህ የንብረት ክፍፍል ኑዛዜ
አይኖረኝም። ግን አንድ ትልቅ የአደራ ኑዛዜ አለብኝ። መስራት የነበረብኝና ሳልሰራው ሞት የቀደመኝ ትልቅ
ቁምነገር ስላለ ልናዘዘው አሰብኩ። ይህን አደራዬን ከእኔ
በኋላ በዚህ ምድር ለምትቀሩት ጓዶቼ በኑዛዜ መልክ
አውርሻችሁ እሄዳለሁ። በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት ኢሕአፓ
ሁለት ስም ይዞ ይገኛል። ሁለት ዴሞክራሲያ፣ ሁለት
ታሪክ ፣ ሁለት አመራር፣ ... ሁለት ... መግለጫ ...።
በዚህም የተነሳ የድርጅቱ እውነተኛ ደጋፊዎች
ከፓርቲው ርቀው ይገኛሉ። ብዙ በዚህ ፓርቲ እምነት
የነበራቸው አባላት ተስፋቸውን ቆርጠዋል። አንዳንዶቹ አልፈው ተርፈው ጥላቻ ደረጃ ደርሰዋል። ዛሬ በዚህ
ኑዛዜዬ ይህ ነው ጥፋቱ፣ ይህ ነው ልማቱ ብዬ ማንንም
ለመውቀስ አልፈልግም። ዛሬ የመጨረሻዬን እስትፋሴን
በምጠብቅበት ወቅት ኢሕአፓ አንድ ሆኖ ተመልሶ
ለማየት እግዜር ስላላበቃኝ አዝናለሁ። ዛሬ ፓርቲው
አንድ ሆኖ ሳልመለከት መስዋትነት የከፈሉትን ጓዶችን በቅርብ እቀላቀላለሁ። ከተሰዉት ጓዶች ጋር በሰማይ
ቤት ስንገናኝ ጥያቄም እንደሚኖራቸው አስባለሁ።
ፓርቲያችን ምን ደረሰ? ብለው እንደሚጠይቁኝ
አምናለሁ። እስቲ ሁላችሁም በእኔ ቦታ ሆናችሁ
መልሱን ፈልጉ። እንደኔ ጭንቀት እንደሚይዛችሁ
አልጠራጠርም። እኔ ዛሬ ለእነርሱ መልስ የሚሆን ማግኘት አለብኝ። ዶክተሩ እንደነገረኝ በዚህ ምድር
የቀሩኝ ቀናት ትንሽ ናቸው። ብዙዎቻችሁ በእኔ ቦታ
ስላልሆናችሁ እንደኔ ላይጨንቃችሁ ይችላል።
ምንአልባትም ስለዚህ ጉዳይ አታስቡ ይሆናል። ግን
ደግሞ ይህ ድርጅት፣ የዚህ ድርጅት ዓላማ የሙታን
አደራ ነውና ይህንን ካላሰብን ምኑን ሰው ሆንነው? ዛሬ ለእነርሱም ምን አድርገህ መጣህ ቢሉኝ ለመመለስ
ይረዳኝ ዘንድ አንድ ኑዛዜ ለመጣል አሰብኩ። በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ፓርቲው አንድ
የሚሆንበትን መንገድ ብቻ ፈልጉ፣ ታገሉ፣ በስሙ
መስዋዕትነትን የከፈሉትን ልታደርጉላቸው የምትችሉት
በብስለት የተፈጠረውን ልዩነት ፈታችሁ ሀገራችሁ ወደ
ነፃነት ጎዳና ልታደርሷት ትችላላችሁ ብዬ አምናለሁ። ለእኔ ግን አንድ ቁም ነገር እንድታደርጉልኝ
እጠይቃለሁ። በመቃብሬ ላይ የሁለቱም አመራር
ተወካዮች እንዲገኙልኝ አድርጉልኝ። ምን አልባት
መሣፈሪያ ችግር ካለ፤ ካለኝ ትንሽ ገንዘብ ላይ
ይሰጣቸው። ይህንን ከፈጸማችሁልኝ በሕይወት
ያልፈጸምኩትን በመቃብሬ ላይ እንደፈፀምኩት እቆጥራለሁ። ለጓዶቼም ይህንን አድርጌ መጣሁ ማለት
እችላለሁ። በዚሁ አጋጣሚ እኔም ከተሰዉት ጋር
ተቀላቅዬ ውጤቱን እጠብቃለሁ። ሠላም ለእናንተ ይሁን!
እንደምታቸንፉ አልጠራጠርም! ... ኑዛዜውን ጽፎ ወደ ግጥሙ ተመለሰ። ምንም እንኳን ቆሜ ባላጫውታችሁ፣
እጄንም ዘርግቼ ሠላም ባልላችሁ፣
አቅፌና ስሜ ከቤት ባልሸኛችሁ፣
አትርሱ ዓላማዬን ቃል እንደገባችሁ፣
አርባ ቀኔም ቢሆን ከተለየኋችሁ። ግጥሙን ጨርሶ ጽፎ አጣጥፎ ካስቀመጠ በኋላ ሞቱን
ይጠብቅ ጀመር። ከትንሽ ቀናት በኋላ ሕይወቱ አለፈ።
በኑዛዜው መሠረት ከሁለቱም የኢሕአፓ አመራሮች
ተገኝተው የቀበሩ ሥነሥርዓት ተፈጸመ። ዛሬ በሁሉም
አባላት ላይ የሙት ኑዛዜ ጩኸት ይሰማል። ኑዛዜዬን
የት አደረሳችሁት? ይላል። እኛስ ይህንን የተሰዉ ጓዶቻችንን ጥያቄ ከምን
አደረስነው? ማሳሰቢያ ፦ ይህ ጽሁፍ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው። ሌንጮ በሰሜን አሜሪካ ዳላስ
ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ ሲሆን፤ ከመሞቱ በፊት
ካደረገው ኑዛዜና በአርባው ላይ እንዲነበብለት
ከጻፈው ግጥም በመነሳት በእውነተኛ ታሪክ ላይ
የተመሠረተ ልብ ወለድ ነው። በልጂግ ዓሊ
መስከረም ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ሎንዶን
|