ልጅ ወልደው መሳም የሚፈልጉ ሴቶች
የሚያዘወትሯቸውን መጥፎ ተግባራት ማስወገድ
እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በእርግዝና ወቅትም ጎጂ ነገሮችን አለማድረግ
ፅንሱ እናቱን እንዲያመሰግን የሚያስችል ሲሆን
ለእናትም ጤናን ይሰጣል ነው የሚሉት
ባለሙያዎቹ፤ ገንዘብንም ይቆጥባል ተብሏል፡፡
በመሆኑም ልጅ ወልዳ መሳም የምትፈልግ
እናት ከሚከተሉት አምስት መጥፎ ልማዶች
መራቅ ይገባታል፡፡
1. ሲጋራ ማጨስ
በእርግዝና ወቅት ከሚያጋጥም የተዛባ የደም
ዝውውር፣ የአተነፋፈስ ችግር፣ የሳንባ ጉዳት
በመጠበቅ ፅንሱ ተገቢውን ደም፣ ምግብ እና
ኦክስጅን እንዲያገኝ ለማድረግ ሲጋራ ከማጨስ
መቆጠብ ተገቢ ነው ተብሏል፡፡
ይህም መሆን ያለበት ከእርግዝና በፊት፣
በእርግዝና ወቅት እና ከወሊድ በኋላ ሲሆን፥
ካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ እና ኒኮቲንን በውስጡ
የያዘውን ሲጋራን በመራቅ ለእርግዝና መዘጋጀት
ወሳኝ መሆኑ ተመክሯል፡፡
በእርግዝና ወቅትም እናት እና ልጅ ጤናማ
እንዲሆኑ የሚረዳ ሲሆን፥ በድህረ ወሊድ
ጊዜም በፅንስ ጊዜ የሚያጋጥሙ በሽታዎች
በልጅ ላይ እንዳይከሰቱ፣ ክብደታቸውም ጥሩ
እንዲሆን ያደርጋል ሲል የአሜሪካ የእርግዝና
ማህበር ጠቁሟል፡፡
2. አልኮልን ወይም አነቃቂ ዕፆችን መጠቀም
በእርግጥ በእርግዝና ወቅት አልኮል መጠጣት
ላይ ያለው አተያይ የተለያየ ቢሆንም፥ ራስን
ከአልኮል ማቀቡ ለጤና መልካም መሆኑን
ብዙዎች ያሰምሩበታል፡፡
የአሜሪካው የእርግዝና ማህበር በበኩሉ አልኮል
ከእናት የእንግዴ ልጅ አልፎ በልጅ ወይም
በፅንሱ ላይ ጉዳት ያስከትላል ነው የሚለው፡፡
ይህም ማለት አበው ሲናገሩ "የሚታይ እንጂ
የማይበላ ፍሬ" እንዲሉ የማይወለድን ፅንስ
በአልኮል መጠጥ ማሳደግ እንደ ማለት ነው
ይላል ማህበሩ፡፡
አልኮል መጠጣትን በቅድመ እርግዝና ወቅት
ማቆም ካልተቻለ ጎጂ ልማዱ በእርግዝናም
ወቅት ቀጥሎ፥ ሽሉ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር
ከመደበኛው ጊዜ ቀድሞ መወለድን፣ የፅንስ
መጨናገፍን፣ የህጻኑን ክብደት መቀነስን እና
የእድገት መቀጨጭን ሁሉ እንደሚያስከትል ነው
ያነሳው ማህበሩ፡፡
3. ተገቢ ያልሆነ አመጋገብ
"ሰዎች የሚመገቡትን ይመስላሉ" የሚል
የፈረንጆች አባባል አለ፤ ታዲያ በሆዷ ውስጥ
ሰውን ያህል ፍጡር የተሸከመች እርጉዝ እናት
ከእርግዝናዋ በፊትም ሆነ በእርግዝናዋ ወቅት
አመጋገቧን መለየት አለባት፡፡
በተለይም ከእርግዝና በፊት የተገኘውን ሁሉ
የመመገብ ልማድ ካላት፥ በእርግዝና ወቅት
ጣጣ እንዳያስከትል ጥንቅቄ እና ውሳኔ ማድረግ
ያስፈልጋታል፡፡
በመሆኑም አንዲት እርጉዝ እናት በእርግዝና
ወቅትም ሆነ ከእርግዝና በኋላ ስላለው ተገቢ
እና የተመጣጠነ አመጋገቧ ትኩረት ማድረግ
ይኖርባታል፡፡
አትክልት እና ፍራፍሬን፣ ጥራጥሬ ምግቦችን፣
ፕሮቲኖችን እና ሌሎችም ገንቢ እና ኃይል ሰጪ
ምግቦችን መውሰድ ለራሷም ሆነ በሆዷ ውስጥ
ላለው ልጇ ጤና ፋይዳው ብዙ ነው፡፡
ከፍተኛ የሆነ የሶዲየም እና የስኳር መጠን
ያላቸውን ምግቦች፣ በማምከኛ ውስጥ ያልገቡ
የስጋ እና ወተት ተዋፅኦዎችን እና በአግባቡ
ያልታጠቡ ምግቦችን እንድትጠቀም
አይመከርም፡፡
4. ከመጠን በታች ወይም ከመጠን ያለፈ
የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ
አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ለእለት ተዕለት
ጤናችን መልካም ነው፡፡
ከፍተኛ የስብ መጠንን ለማስወገድ፣ የስኳር
በሽታን ለመቀነስ፣ ኃይል እና ጥንካሬን
ለመጨመር፣ የጀርባ ህመመን ለማስታገስ ሁሉ
ይረዳል፡፡
ሆኖም በጣም አድካሚ በሌላ በኩልም በጣም
ትንሽ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ጉዳት
ያስከትላል፡፡
በተለይም ሴቶች ከመጠን በላይ የሆነ የአካል
እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ፥ እንቁላል
እንዳያመርቱ፣ የወር አበባም እንዳያዩ በማድረግ
የእርግዝና ህልማቸውን ሊያቀጭጭባቸው
ይችላል፡፡
በጣም ትንሽ የአካል እንቅስቃሴ ደግሞ
ለውፍረት እና ለስኳር በሽታ ሊያጋልጥ
እንደሚችል፥ ይህ ደግሞ ሴቶች እንዳያረግዙ
የሚያግድ ሌላ ጣጣ እንደሚያመጣባቸው
ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም ልጅ ወልደው መሳም የሚፈልጉ
ሴቶች በአቅማቸው ልክ፥ በተለይም እስከ 30
ደቂቃ የሚደርስ የተመጠነ የአካል እንቅስቃሴ
ማድረግ እንዳለባቸው ነው ባለሙያዎች
የሚመክሩት፡፡
5. ድካም ሲኖር እረፍት አለማድረግ
የትኛዋንም እናት ብትጠይቁ ልጅ ማሳደግ ከባድ
ኃላፊነት ነው፤ በመሆኑም ለሆርሞን ምጣኔ እና
ለማንኛውም ጤና እንደ እናት እረፍት
ያስፈልጋታል ይላል የአሜሪካው ብሔራዊ
የእንቅልፍ ፋውንዴሽን፡፡
በመሆኑም በየቀኑ በትንሹ ለ20 ደቂቃ
የእንቅልፍ ሸለብታ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡
በመሆኑም አንድ እርጉዝ ሴት ድካም ሲሰማት
በደመነፍስ የእግር ጉዞ ከማድረግ ይልቅ
ሸለብታን የግድ መጠቀም አለባት የሚል ምክር
አለው ፋውንዴሽኑ፡፡
ምንጭ፡-http://health.howstuffworks.com/
በምህረት አንዱዓለም & fanabc.com
|