የፍቅር ቀጠሮ
ከታገል ሰይፉ©ለድሬቲዩብ ጠበቅኩሽ እኔማ-
እዚያው ሥፍራ ቆሜ
በአክሱም ቁመና- በላሊበላ ዕድሜ
እግሮቼን ተክዬ-ቀኔን አስረዝሜ
በሔድሽበት መንገድ- ልቤ እንደነጎደ ስንት ነገር መጣ-ስንት ነገር ሄደ
ስንት ጊዜስ ነጋ- ስንቴ ጎህ ቀደደ ስንቴ ዝናብ ጣለ-
ስንት ጊዜ አባራ
ትመጫለሽ ብዬ -በቆምኩበት ሥፍራ
ስንቴ አድማሱን ማተርኩ-ስንትና ስንት ዓመት
አንገቴን አስግጌ-በራስ ዳሽን ቁመት በአክሱም ቁመና- በላሊበላ ዕድሜ
በቀጠርሽኝ ሥፍራ-ስጠብቅሽ ቆሜ ስንት ሳቅ አለፈ-
ስንትና ስንት ዕንባ
ስንቴስ ክረምት ሆነ-ስንቴ ፀደይ ጠባ
ስንቱ ተገናኘ-ስንቱ ሰው ተጋባ
ሽል ስንቴ ልጅ ሆነ-ስንትስ ጊዜ አረጀ ስንት ኮት ጨረሰ- ስንት እንጀራ ፈጀ
ስንት ዓይነት ሞት አየሁ- ስንት ዓይነት ፍፃሜ
በአክሱም ቁመና-በላሊበላ ዕድሜ
በቆምኩበት ሥፍራ-ስጠብቅሽ ቆሜ?
ስንት ውበት አለፈ-ስንት ውበት ነጎደ
ስንት ትውልድ መጣ -ስንት ትውልድ ሄደ ስንት ዕውነት ከፍ አለ-ስንት ዕውነት ወረደ
ስንት ዓለም ተሻረ- ስንት ዓለም ነገሠ ስንት ሀገር
ተሰራ-ስንት አገር ፈረሠ
ስንት ሺህ ዓመት ሸኘሁ-ስንት ሺህ ተቀበልኩ
እዚያች ሥፍራ ቆሜ-አንችን እየጠበቅኩ
እግሬን አስረዝሜ-ቆየሁ ቆየሁና በላሊበላ ዕድሜ- በአክሱም ቁመና
ሳትመጪ ወደኔ-ሳላገኝሽ ገና ብዙ ነገር መጥቶ -ብዙ
ነገር ያልፋል
የራስ ዳሽን ራስ-አንገቱን ይደፋል
አክሱምም ተንዶ- እንደጨው ይረግፋል
ላሊበላም ወርዶ-ቁልቁል ይነጠፋል ሰማይና ምድርም ያልፋሉ ታያለሽ
እኔ ግን እዛው ነኝ-አንች እስክትመለሽ…
|